ኪዳነ ምሕረት
ኪዳን የሚለው ቃል ‹‹ቃል›› ከሚለው ጋር እየተዛረፈ በብሉይ ኪዳን ለ280 ጊዜ ያህል ሲጠቀስ በአዲሰ ኪዳን ደግሞ ከ32 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ኪዳን›› ቃሉ ‹‹ተካየደ›› ተማማለ፣ ቃል ተገባባ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹ምሕረት›› የሚለው
ቃል ደግሞ ማብራሪያ ሳያሻው ምሥጢሩ ከነዘይቤው ከግእዝ የተወረሰ ነው፡፡ ስለዚህ ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ከተራ ውሎችና ስምምነቶች የበለጠ ጽኑና ቀዋሚ ነው፡፡ ከፍ ያለ ክብደትም አለው፡፡
‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አድርጋለሁ›› ተብሎ በዳዊት መዝሙር እንደተጻፈ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ ወደፊትም ያደርጋል፡፡ (መዝ88.3) ቃል ኪዳኑም የምሕረት ቃል ኪዳን ነው፡፡
በቅዱሳን አበውና በቅዱሳት እማት እናቶች ታሪክ፣ ገድልና ድርሳን እንደምናነበው እግዚአብሔር ለቅዱሳን ከመሞታቸው አስቀድሞ ይገለጥላቸውና የምሕረት ቃል ኪዳን ይሰጣቸው ነበር፡፡ የእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን በቅዱሳኑ ሕይወት ዙሪያ ብቻ የሚያተኩር አይደለም፡፡ ለስማቸው፣ ለመስቀላቸው፣ ለልብሳቸው ገድላቸውን ከትቦ ለያዘ መጽሐፍ፣ አልፎ ተርፎም ለረገጡትና አፈርና ለተጋደሉበት ቦታ ሁሉ ተርፎላቸዋል፡፡ ስለዚህ ልዩ ልዩ ቃል ኪዳን የተገባላቸው ቅዱሳት መካናት ሞልተዉናል፡፡
‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳኔን አደርጋለሁ›› ባለው መሠረት ጌታ ከእመቤታችን ጋር ብዙ ቃል ኪዳን አድርጓል፡፡ እርሷ የተመረጠች ብቻ ሳትሆን ከተመረጡትም ሁሉ የተመረጠች ናትና፡፡ ከቅዱሳን ሁሉ እመቤታችን ድንግል ማርያም በሁሉም ረገድ እንደምትበልጥ ከተሰጣቸውም የምሕረት ቃል ኪዳን ለሷ የተሰጣት ኪዳን በእጅጉ ይበልጣል፡፡ በዚህም ምክንያት ድንግል ማርያም በተሰጣት ቃል ኪዳን ተለይታ ትታወቃለች፡፡ ማለትም ትጠራበታለች ኪዳነ ምሕረት ትባላለች፡፡ ስለዚህ የኃጥአን ሁሉ ዓይን የእርሷን የምሕረት ቃል ኪዳን ተስፋ ያደርጋል፡፡
Recent Sermons
የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የአባልነት መመዝገቢያ ቅፅ
March 30, 2018
ቤተክርስቲያናችን እንደ ተቋም በሃገሩ ህግ የተመዘገበችበት
March 29, 2018
እግዚአብሔርን መፍራት
February 17, 2018