ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን

ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን

በመሠረቱ ምሥጢር ሲባል ለተወሰነ ሰው ብቻ የሚነገር ሁሉ ሊሰማው የማይገባ በወዳጅ ዘንድ በምሥጢርነት የሚቆይ ለሌላ የማይገለጥ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ለተለዩና በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባሉ በጥምቀት ለከበሩ ብቻ እንጂ ለማንም የማይሰጥ እንዲሁም ላመኑት ብቻ ፀጋንና ረቅቅ ሀብትን የሚያሰጥ ስለሆነ ነው፡፡ በሜቴ 13፡11 ጌታ ትምህርቱን በምሳሌ ሲያስተምር ሐዋርያት ጌታን ለምን በምሳሌ ታስተምራለህ? ቢሉት ‹‹ ለእናንተ ምሥጢርን የማወቅ ፀጋ ተሰጥቷችኋል ለነሱ ግን አልተሰጣቸውም›› በማለት እነዚህን ምሥጢራት ለሁሉም እንደማይነገሩና ግልጽ እንደማይሆኑ አስረድቶናል፡፡

ምስጢር፡- ሲባል በዓይን የማይታይ በእጅ የማይጨበጥ ተመርምሮ የማይደረስበት በእምነት ብቻ የሚቀበሉት ማለት ነው፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንም ከፍ ያለ ጸጋን የሚያሰጡት እንዴት እንደሆነ ስለማይታይ እና ስለማይታወቅ ምሥጢር ተብለዋል፡፡

እነዚሀም ምሥጢራት በጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ መሥራችነት የተመሠረቱ ሲሆን ጸጋንና በረከትን የሚያስተላልፍባቸው ራሱ በዕለተ ዓርብ ካደረገው የማዳን ሥራ የመነጨ ይህም የማዳን ሥራ እስከ ዘለአለም ኃይሉ የሚታወቅባቸው ታላላቅ ምሥጢራት ናቸው፡፡

7ቱን ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንም 7 መሆቸው በመጽሐፈ ምሳሌ 9፡1 ላይ ‹‹ጥበብ ቤቷን ሠራች ሰባቱንም ምሰሶዎችዋን አቆመች›› ይላል፡፡ ጥበብ የተባለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ሰባት ምሰሶች የተባሉት ደግሞ የ7ቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ነው፡፡ እነዚህም

  1. ምሥጢረ ጥምቀት፡- መንፈሳዊ ልደት
  2. ምሥጢረ ሜሮን፡- መንፈሳዊ ዕድገት /በመንፈስ ቅዱስ መበልጸግ/
  3. ምሥጢረ ቁርባን፡- መንፈሳዊ ምግብ /የዘለአለም ሕይወት/
  4. ምሥጢረ ንስሐ፡- መንፈሳዊ ድኅነት /ሥርየተ ኀጢአት/
  5. ምሥጢረ ተክሊል፡- የጋብቻ ጽናት
  6. ምሥጢረ ክህነት፡- የማሠርና የመፍታት ፣ የማስተማር ፣ የማደስ ፣ የማጥመቅ ፣ ሥልጣን /መንፈሳዊ ኃይል/
  7. ምሥጢረ ቀንዲል፡- ሥጋዊና መንፈሳዊ ኃይል /ከበሽታ መፈወስ/

እነዚህ ምሥጢራት በቤተክርሰቲያን ውስጥ በሚታይ ሥርዓት የማይታዩ ጸጋን ሥልጣነ ክህነት ባላቸው አባቶች የሚሰጡ መንፈሳዊ ሀብት ናቸው፡፡ ከሰው አስተሳሰብ በላይ ስለሆኑ እግዚአብሔር ካልገለጸልን በቀር መርምረን አንደርስበትም ከፍፃሜያቸው አንዘልቅም፡፡ በዚህም ሥርዓት ዲያቆናት በአገልግሎት ሲራዱ ቀሳውስት ደግሞ ሜሮን ከማፍላትና ክህነትን ከመስጠት ውጭ ሁሉን ይፈጽማሉ፡፡ ጳጳሳት ሁሉን ምሥጢር በመፈጸም ያገለግላሉ፡፡

share

error: Alert: Content is protected !!